Books, Book reviews, Film reviews
Short stories, and more

STIFHAB

BOOKS AND FILMS

የጋዜጠኛው ማስታወሻ 
ትሰፋዬ ገ/ አብ
ሃያሲ / መኮንን ገ/እግዚ (ፓስ) 

''አንድ ቀን ባህላቸውንና ወተታቸውን እየመገቡ ወዳሳደጉኝ የረርና ከረዩ ገበሬዎች እንደምመለስ መንፈሴ ዘወትር ሹክ ይለኛል። ወደ ሃገሬ ተመልሼ፣ በቢሾፍቱ ሃይቅ ዳርቻ ወይም በዝቁዋላ ተራራማዎቹ አካባቢ የራሴን ጎጆ እቀልሳለሁ። በጎችና ዶሮችም አረባለሁ። የምወዳቸውን ዘፎች በግቢዬ ውስጥ እተክላለሁ። መጻህፍትንም በብዛት እጽፋለሁ።  
ምን ጥያቄ አለሁ?
እኔ ንደሁ ትናንት ቢሾፍቱ ነበርኩ። ነገም ቢሆን ቢሾፍቱ ነኝ ከነግ ወዲያ ማናችንም በህይወት አንኖርም። በታሪክ በብጎ የመታወስ መብት (ዋስትና)  ያለው ከቶ የለም''


በማለት ነው ደራሲ ተስፋዬ የጋዜጠኛው ማስታወሻ በተሰኘው መጽሀፉ የጀመረውን እጅግ አስገራሚ ታሪክ የሚያጠናቅቀው።
------------------------------------------------------

ይህ ስራ--- የታሪክ አወቃቀሩ፣ የቁዋንቁዋው ጥራት፣ የአተራረክ ስልቱና ግልጽነቱ፣ መጽሀፉን ከዚህ በፊት ከታዩት እንደ አጥፍቶ መጥፋትና ኦሮማይ አይነት ማስታወሻ መሰል ስራዎች የተለየ ያደርገዋል። አጥፍቶ መጥፋት ከደርግ ውድቀት በሁዋላ ሰለተጻፈ ደራሲው ምንም አደጋ ባላጠላበት ሁኔታ የጻፈው ሲሆን ኦሮማይ ግን በስርአቱ ስር እያለ ደራሲው በተቻለ ህልውናውን አደጋ ላይ ባለመጣልና ማሰተላለፍ የፈለገውን እውነታንም ባለማዛበት መሀል ሚዛን ጠብቆ የጻፈው ነው ማለት ይቻላል። የጋዜጠኛው ማስታወሻ ለየት የሚለው ከአገር ውጭ በመጻፉ ሲሆን በትረካው የሚያጋልጣቸው ሰዎች እሁንም በስልጣን ላይ ያሉ ናቸው። ተስፈዬ ለበቀል እርምጃ ሰለ መጋለጡ የሚታውቅ ነገር የለም። ከህይወት እጣፈንታው አንዱ ይህን ታሪክ መተረክ ስለነበር በተለያየ አጋጣሚ፣ ከተለያየ አቅጣጫ በህልውናው ላይ የተሰነዘሩበትን ፈታኝ ጥቃቶች አምልጦ በኢትዮጵያ ስነጽሁፍ ታሪክ ውስጥ የራሱን የክብር ቦታ የሚይዝ ታሪክ ለመስራት በቅቶአል። አሁንም ይህን የቃላት ኣዳፍኔ ወርውሮ እዛው ከወረወረበት ጉዋሮ ቁጭ ብሎ ይጥብቃል ብዬ አልገምትም። ወርውሮ ዞር እንዳለ ነው የሚሰማኝ።

በአራት መቶ ገጻት ውስጥ ደራሲው ከልጅነት አስከ አሁኑ ጊዜ የገጠሙትን አበይት የሚላቸውን ክዋኔዎች ልቅም አድርጎ በጣፋጭ ቃላት ከሽኖ ሲያቀርብ የዘመንን ቅደም ተከተል chronological order አልተከተለም። ታሪኩን በአስራ ዘጠኝ ዐምት እድሜው ስራ ፍልጋ ሲወጣ ጀምሮ፣ መሀል ላይ ወደ ልጅነት ዘመኑ ይመልሰንና ህይወቱ አሁን ወዳለችበት አቅጣጫ እንድትታጣፍ ምክንያት ስለሆኑት ወላጆችና መምህራን ይነግረናል። ከመደምደሚያው የሚደርሰው እንደያስፈላጊነቱ ወደ ሁዋላና ወድፊት እየቃኘ ነው። ከአንድ መሳጭ ክፍለ ታሪክ ቀጥሎ ቀልድ ለበስ አስቂኝ ትረካ፣ ከአንድ አስገራሚ የፖለቲካ ሽፍጥ በሁዋላ አዝናኝ የፍቅር ታሪክ። ካስጨነቀን በሁዋላ እያዝናናን፣ ከሳቀን በሁዋላ እያሳዘነን። 

ይህ የአጻጻፍ ዘዴ አንባቢና መጽሀፉ ሳይሰላቹ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ የሚያደርግ ዘመናዊ የአጻጻፍ ስልት ነው። አንባቢያን መጽሀፉን መጀምር ብቻ ነበር ችግራችን። ከዚያ በሁዋላ ያለው ስራ የመጽሃፉ እንደሆነ ነው የገባኝ። ከጀመሩት የማይለቅ መጽሀፍ። 

የጋዜጠኛው ማስታወሻ የሚደነቅበት ሌላው ገጽታ ቁዋንቁዋው ነው። አማርኛው። አማርኛ የመንግስት ቁዋንቁዋ ከሆነ ቢቆይም ባለፉት ሁለት መንግስታት ዘመን አቅሙ ከሚፈቅድለት በላይ አንዲያገለግል የተገደደበት ጊዜ ነበር። ደርግ ሶሸሊዝም የተሰኘውን ባእድ ርእዮተ ዓለም የሀገሪቱ መመሪያ እንዲሆን ካወጀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተገረሰሰበት ወቅት ድረስ አማርኛ ዲያሌቲክስን የመሰለን ረቂቅ ጽንሰ ሀሳብ እንዲገልጥ፣ ዳስከፒታልን ከሚያክል ውስብስብ ጥናት እንዲተረጉም ያልተሞከረበት ነገር አልነበረም። ገላጭ ቃል ፍለጋ ከግእዝ እስከ እንግሊዝኛ ያሉት ቁዋንቁዎች ተፈልቅቀው ተፈትሽዋል። 

ርእዮተ ዓለም
ቀኝ መንገደኛ
ኢሳይንሳዊ ወዘተ

የሚባሉ ቃላት የተደመጡት በደርግ ጊዜ ነበር።

አሁን ያለው ስርአትም የፌዴራሊዝምን ፍትሀዊነት ለማብራራት፣ ብሄረሶችን የመገንጠል መብት ለመስበክ፣ ውሽቱን ውነት፥  እውነቱን ወሽት ለማስምሰል ቁዋንቁው ላይ ያልሞከረው ነገር የለም። አዲስ ሃሳብ ለመግለጥ አማርኛን ሲለጥጠውና ሲቆለምመው ይደመጣል።

አናሳ ብሄር
ሙስና፣
ገጠርን ያማከለ
የፈንጂ ወረዳ ወዘተ

መባል የተጀመረው በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ነው።

የደራሲ ተስድፋዬ መጽሀፍ ግን ያን አይነት ችግር አላየሁበትም። የተጠቀመው ቀላል የንግግር አመርኛ ሲሆን፣ የገለጸው ሀስብ ግን ጥልቅ ነው።

ምሳሌ

  • በእኛና በነሱ መሃል ውጊያ ከተጀመረ ያቺ ምድር በሀበሻ ደም ትጨቀያለች።


  • አምዴና እኔ እንግባባ ነበር። ያን ከተነጋገርን በሁዋላ (እጃቸውን ለወያኔ የመሰጠት ነገር ተነጋግረው ነበር።) እኔ እርምጃዬ ስቀንስ፣ እሱ ፍጥነቱን ጨመረ። በዚያ ተለያየን።


ተስፋዬን በጣም ተነባቢ ያደረገው አንዱ ይህ ጥልቅ ሀሳባትን በቀላል ቁዋንቁዋ የመግለጽ ችሎታው ይመስለኛል።

ሌላው መጽሀፉን ተነባቢና መሳጭ ያደረገው የልቦለድ አጻጸፍ ዘይቤ መከተሉ ነው። በእውነተኛ ዘገባ ወይም ማስታወሻዎች አጻጻፍ ያልተለመደ የአካባቢ ገለጣ፣ የባለታሪክን ባህሪያት መሳልና ቀጥተኛ ጭውውቶችን በተሳካ ሁኔታ ተጠቅሞባቸዋል። በተለይ ጭውውቱ ለትረካው ጣእመ ልቦለድ የሰጠው ዋና ከፍል ነበር ማለት ይቻላል። ደራሲው ከገለጣ ወደ ጭውውት፣ ከጭውውት እንደገና ወደ ገልጣ የሚያደርገውን ሽግግር ንባብን በማያደናቅፍ መልኩ ያመቻቸበት ዘዴም ሳይጠቀስ የሚያልፍ አይደለም። 

በተረፍ ደራሲው በትረካው ውስጥ አልፎ አልፎ የግሉን አመለካከት በሰበካ መልክ መወተፉን አልወደድኩለትም። ሁለንተናዊ እውነታ ወይም ተፈጥሮወዊ ህግጋት ካልሆኑ በቀር ደረሲው የግሉን እምነት እንደማይገሰስ ቃለ መለኮት ሲያሰፍር ትረካው ግራዋ ግራዋ ሊል ይችላል።


ምሳሌ

ህወሀት ለስልጣኑ ህልውና መረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ መስሪያ ቤቶችን መያዙ የሚጠበቅ ነው። ውጭ ጉዳይ፣ ደህንነት፣ ጠ/ሚንስትርና መከላከያን ከለቀቀ ህልውና አይኖረውምና ማንም ቢሆን ይህን ይገነዘባል። ህወሀት ህልውናውን ከማስጠበቅ ባሻገር ለሀገሪቱ እድገት ሲል እንኩዋ ከዚያ በመለስ ያሉ ሙያ ነክ የስልጣን ቦታዎችን ለባለሙያ መተው አለመቻሉ ነው ችግሩ።


ይህ የደራሲው ግለዊ አመለካከት ነው። አቀረረቡ እንደ ስበካ ነው። ህወሀት ያግበሰበሰው ስልጣን ለህልውናው የሚያስፈልገው ስለሆነ ይገባዋል፣ የሚል አንደምታ ያለው ሀሳብ ይመስላል። ደራሲው የግሌ አመልካከት ብሎ ቢያስቀምጠው ቅሬታ አይኖረኝም። እንደ ዐለምዐቀፋዊ እውነታ (UNIVERSAL TRUTH) ቁጭ ማድረጉ ላይ ነው፣ችግሩ። 

በተረፈ እኔ በግሌ ... ይህን ስራ የማይው እዚህ ስራ ላይ ከሰፈርው ሀሰብና ሀሳብ ብቻ በመንሳት ነው። የደራሲው የቀድሞው ስራና እዚያ ላይ የሰፈረው ጉዳይ በጣም የረበሻቸው አንባቢያን ታዝቤአልሁ። ለዚያ ደራሲው የሚሰጠው መልስ ይኖር ይሆናል። ደራሲው ከኤርትራ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ከመጡ ሰዎች መወለዱ ያቅለሸለሻቸው ጎጠኞች ለሰነዘሩበት ዘለፋ ግን ቅንጣት ታህል ትኩረት ይሰጠዋል ብዬ አልገምትም። ደራሲው ኢትዮጵያዊነቱን የሚሰጠው ሆነ የሚነጥቀው ምንም ሀይል እንደሌላ ራሱ ተናግሮአል። 

በኔ እምነት ኢትዮጵያዊነት ዜግነት ብቻ አይደለም። እውስጡ ከህልውናና ከማንነት ጋር የተያያዙ ብዙ እሴቶች አሉት። ኢትዮጵያዊነት አይሰጥም፣ አይነጠቅም፣ አይበላለጥምም። ባራክ ሁሴን ኦባማ የአሜሪካን ፕሬዝደንት በሆነበት በዚህ ዘመን ከጉልታዊነት በታች ዘቅጠው የዘር ጥያቄ የሚያነሱ እዛው በዘቀጡበት ተጉነፍንፈው እንዲቀሩ መተው እንጂ ከነሱ ጋር እስጥ አገባ አያስፈልግም። 

ለማጠቃለል ያህል ለጋዜጠኛው ማስታውሻ ከ 5 ውስጥ 4.5 ዛፍ ስጥቼ 
P P P P p 

Oops! This site has expired.

If you are the site owner, please renew your premium subscription or contact support.