Books, Book reviews, Film reviews
Short stories, and more

STIFHAB

BOOKS AND FILMS

የህፃናት ኣምባ
______________________

የአስትሪድ ተረቶች

አስትሪድ ሊንድግሬን

አስትሪድ ሊንድግሬን በስዊድን አገርና በአለም ዓቀፍ ህብረተ-ሰብ ከፍተኛ ዝናና አድናቆት ያተረፈች ደራሲት ነበረች። አስትሪድ የምትታወቀው የልጆች መጻህፍት በመድረስ እንደሆነ ሁሉ የትያትርና ፊልም ተውኔቶች በመጻፍም በዓለም ተወዳጅና ዝነኛ ነበረች። ከፊልምና የሬዲዮ ድራማዎች ውጭ 40 የሚሆኑ መጻህፍትና በርከት ያሉ የትያትር ተውኔቶች ለንባብና ለእይታ አብቅታለች። መጻህፍትዋ ከ95 በማያንሱ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች የተተረጎሙ ሲሆን እአአ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ 145 ሚሊዮን ያህል መጻሀፍት ታትመው ተሸጠዋል።

አስትሪድ በስራዎችዋ ብዙ ከፍተኛ ክብር ያላቸው ብሄራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ሸልማቶች አግኝታለች። ከሸልማቶችዋ መሃል የስዊድን አካዳሚ ታላቁ የወርቅ መዳሊያ አንዱ ሲሆን የሊንሸፒንግ ዩኒቨርስቲ፣ የሌሲስተር ዩኒቨርስቲና የዋርሶ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክተር ማዕረግ ሰጥዋታል። በስምዋ የሚታደሉ በርካታ ሽልማቶችም ተሰይሞላታል። ከነዚህ አንዱና ትልቁ አምስት ሚሊዮን ክሮነር (15 ሚሊዮን የኢት ብር) የሚያስገኘው “የአስትሪድ ሊንድግሬን ማስታወሻ” የስነጽሁፍ ሸልማት ነው። አስትሪድ

4መጻፍ ከጀመረችበት 1940 እሰከ 2001 ዓ ም ድረስ 48 የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሸልማቶችን አግኝታለች።

አስትሪድ ህዳር 14 ቀን 1907 ዓ ም ስዊድን ውስጥ በስሞላንድ አውራጃ ልዩ ስሙ ቪመርቢ በሚባል ሰፈር ተወለደች። መጻፍ የጀመረችው በ1940 ዓ ም ሲሆን፣ የመጀመሪያ ስራዋ ህመምተኛ ልጅዋን ስታስታምም ታወራላት የነበረው “ፒፒ ባለ ረጅም ሹራቡዋ”” የተሰኘው ዝነኛው ተረት ነው። አስትሪድ እስከ 90ዎቹ መሃል ድረስ መጻፍ ሳታቋረጥ ሰርታ ጥር 28 ቀን 2002 ዓ.ም በ94 ዓመት ዕድሜዋ አረፈች። አስትሪድ ከዚህ ዓለም በሞት ብትለይም በስራዎችዋ ግን ሁሌም ህያው ሆና በአድናቂዎችዋ በተለይም በህጻናትና ወላጆች ልብ ውስጥ ትኖራለች።


///////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////

ተረተ ተረት 

ኒልስ ሚጢጢው
አስትሪድ ሊንድግሬን
የልጆች መጽሐፍ


ኒልስ ካርልሶን-ሚጢጢው


በርቲል መስኮት አጠገብ ቆሞ ወደ ውጭ ተመለከተ። እናቱና አባቱ ከሥራ እስኪ መለሱ እየጠበቀ ነው። ደጁ መጨለም ጀምሯል። መንገዱንም ጉም ሸፍኖታል። ብርዳም የሚያሰጠላ ቀን ነው። እናቱና አባቱ በየቀኑ ወደ ሥራ ሲሄዱ እሱ እቤት ውስጥ ብቻው ይቆያል። ሲርበው የሚበላውን ምግብ እናቱ አዘጋጅታ ትሄዳለች፣ ግን ብቻውን ሲሆን አይበላለትም፣ ወላጆቹ ሲመጡ ነው፣ ራቱን በደንብ የሚበላው።


አቤት ጊዜው እንዴት ይንቀረፈፋል! ደጅ ወጥቶ ከልጆች ጋር መጫወት የሚከለክለው የለም፣ ግን በብርዱ ወራት ሊጫወት የሚወጣ አንድ ልጅ የለም። ቤት ውስጥ ያሉት መጫወቻዎቹ ደግሞ የቆዩ ናቸው፣ ሰልችተውታል። ለነገሩ እስከዚም ብዙ መጫወቻዎች የሉትም። መጻህፍት ነበሩት ግን ያሉትን በሙሉ ስእላቸውን ደጋግሞ ተመልክቷል። ማንበብ አይችልም፣ ገና ስድስት ዓመቱ ነው።


ቤቱ ይበርዳል። በርቲል በብርድ ተንቀጠቀጠ። ዙሩያ ጥግ ጥጉን ደግሞ መጨላለም ጀምሯል፡ ~አሁን መብራት ማብራት ምን ዋጋ አለው፣ ከብቸኝነት አያድን? ምን ማድረግ ይሻል ይሆን?

ቤርቲል ድብር እንዳለው ወደ አልጋው ሄደና ጋደም አለ። አልጋው ላይ ተጋድሞ ስለ አሳዛኝ ህይወቱ ማሰብ ጀመረ። እንዲህ ሁሌ ብቻውን አልነበረም፣ በርቲል። በፊት አንድ እህት ነበረችው፣ ማርታ ትባላለች። አሁን የለችም። ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። ማርታን እያሰበ፣ ብቸኝነቱን እያብሰለሰለ እንባው በጉንጮቹ ይወርድ ጀመር።


ያኔ ነው ድምፅ የሰማው፡ ከአልጋው ስር የትንንሽ እርምጃዎች ድምፅ። “ጭራቅ?” አለ በርቲል በሆዱ። ወዲያው ወደ አልጋው ጠርዝ ተሳበና አጎንብሶ ወደ ታች ተመለከተ። አንድ በጣም የሚያስደንቅ ትንሽ ፍጥረት ከአልጋው ሥር ቆሟል። ሲያዩት አዎ እንደ ማንኛውም ትንሽ ልጅ ነው፡ ብቻ ይሄ ከእጅ ስንዝር አይበልጥም፣ ቁመቱ። ሚጢጢ ነው።

“ሰላም” አለው ሚጢጢው ልጅ።

”ሰላም”  መለሰ በርቲል፡ በግርምታና በግራ መጋባት።

‘’ታዲያስ” አለ ሚጢጢው በመቀጠል።

በርቲል አልመለሰለትም፣ ብቻ ገርሞት ዝም ብሎ ተመለከተው። ከትንሽ ዝምታ በኋላ “ለመሆኑ ምንድን ነህ?” አለው። “ደሞስ አልጋዬ ሥር ምን ታደርጋለህ?”

“ኒልስ ካርልሶን ሚጢጢው እባላለሁ::” አለ ሚጢጢው “እምኖረውም እዚህ ነው፤ አ… እዚህ አልጋህ ሥር ማለቴ አይደለም፣ አንድ ፎቅ ወደታች ዝቅ ብሎ።”

“አትቀለድ።”

“ሙት! ቀልዴን አይደለም። ከፈለክ መግቢያውን ማየት ትችላለህ… ያው እዚያ ጥግ” በማለት ልጁ አልጋው ሥር ወዳለው የአይጥ ጉድጓድ በጣቱ አመለከተ።

“እዚህ? ኖ! ለመሆኑ ለምን ያህል ጊዜ እዚህ ኖርክ?" በርቲል በመገረም ጠየቀ።

“አይ፥ አንድ ሁለት ቀኖች” አለ ሚጢጢው ልጅ:: “በፊት ሊለያንስ ጫካ ከሚባል ሰፈር አንድ ዛፍ ሥር እኖር ነበር። ግን እንደምታውቀው የበልግ ወራት ሲመጣ፣ የውጭ ኑሮ ያንገፈግፍህና ወደ ከተማ መምጣት ያሰኛሃል።  እንዳጋጣሚ እህቷ ዘንድ የምትቀይር አይጥ አግኝቼ፥ ከእሷ  ይሄን ቤት ተከራየሁ። አልያማ ታውቃለህ፣ ቤት ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው”።


    አዎ ስለ ቤት ችግር በርቲልም ሰምቷል።


‘’ያው ባዶውን ነው የተከራየሁት” ሚጢጢው ማብራራት ቀጠለ ‘’እንዲያ ይሻላል፣ በተለይ የራስህ እቃ ካለህ።” አለና ፈገግ አለ።

“የራስህ እቃ አለህ፣ ታዲያ?”

“የለኝም… እሱ ብቻ ነው ችግሬ” ካለ በኃላ የሚጢጢው ፊት ቅጭም አለ። “ትትት! እዚያ ታች እንዴት ይበርዳል መሰለህ” አለ ሰውነቱን እየተንቀጠቀጠ። “እዚህ አንተምጋ ያው ነው ባክህ።”

“የዘንድሮ ብርድ! ተወው … እኔም አልቻልኩትም።”

“የጡብ ምድጃ ነበረኝ ግን እንጨት ጠፋ። እንጨትም ተወዷል።” አለና ሚጢጢው ራሱን ለማሟሟቅ ወዲያና ወዲህ ተወዛወዘ። ከዚያ በርቲልን ትክ ብሎ እያየው “ለመሆኑ ቀን ቀን ምን ትሰራለህ?” ሲል ጠየቀው።

“ምን እሰራለሁ! ምንም” አለ በርቲል። “ምንም የተለየ ነገር አላደርግም።”

“እኔም” አለ ሚጢጢው፣ “ብቸኛ መሆን ይሰለቻል አይደል?”

“በጣም እንጂ”

“አንዴ… እኔ ቤት ለምን አብረን አንሄድም ታዲያ።” ሲል ሚጢጢው በጉግት ጠየቀ።

በርቲል ሳቁ መጣ። “በዚያች ቀዳዳ ያልፋል ብለህ ታስባለህ?”

“እሱን ለኔ ተወው።  ቀላል ነው፡፡”

“ቀልደኛ ነህ።”

“ቀልድ አይደለም። ቀዳዳው አጠገብ ያለውን ሚስማር ታያለህ፣ እሱን ነካ አድርገህ ‘ሺልቪፐን’ ስትል እንደኔ ትንሽ ትሆናለህ።”

ልጁ የምሩ መሆኑን ሲያይ፣ በርቲል “ወላጆቼ ሳይመጡ ፥እንደገና ትልቅ መሆንስ እችላለሁ?” ሲል ጠየቀው።

“እንዴታ! ያኔም ሚሰማሩን ነካ አድርገህ  ‘ሺልቪፐን’ ማለት ብቻ ነው።

“ወቸ ጉድ! ለመሆኑ አንተስ እንደኔ ትልቅ መሆን ትችላለህ።”

“አዝናልሁ፣ አልችልም።” አለ ሚጢጢው በሃዘኔታ መሬት መሬት እያየ፣ ከዚያ ቀና ብሎ “ግን አንዴ እኔጋ ብትመጣ ደስ ይለኝ ነበር።” አለ።

“በል እሺ እንሂድ” በርቲል ከአልጋው ወረደ። ከዚያ በአልጋው ስር እየዳከ ሄዶ የአይጥ ጉድጓድ መግቢያ አጠገብ ሲደርስ በአመልካች ጣቱ ሚስማሩን ነካና “ሺልቪፐን” አለ። እውነትም እዚያው እንደቆመ ሚጢጢውን አክሎ ቁጭ አለ።

“አላልኩህም! እኔኮ ኒልስ ነኝ” አለና ሚጢጢው እጁን ዘረጋለት።

"በል ና ... ወደ ቤቴ እንውረድ።”

በርቲል በግርምታ እንደተዋጠ በጨለማው ጉድጓድ ውስጥ ለመግባት ቸኮለ ።

“ቀስ። እንዳትወድ" አለ ኒልስ "ደረጃውን ተጠንቅቀህ ውረድ... የእጅ መደገፊያው ሰባራ ነው።”

በርቲል ትንሹን የዲንጊያ ደረጃዎች በቀስታ እየረገጠ ይወርድ ጀመር። እዚህ ሥር ደረጃ ይኖራል ብሎ አሰቦ አያውቅም ነበር። ደረጃው መጨረሻ ላይ አንድ በር አለ። በሩ ተዘግቷል።

“ቆይ መብራት ላብራ” አለና ኒልስ ማብሪያውን ተጫነ። መብራቱ ሲበራ በሩ ላይ የተለጠፈው የአድራሻ ካርድ ታየ፣ ኒልስ ካርልሶን ሚጢጢው ይላል።

ኒልስ በሩን ከፈተና አሁንም አንድ ማብሪያ ሲጫን ጨለማው ተገፎ ብርሃን ሆነ። በርቲልም ገባ። ቤቱ ይበርዳል።

“ይሄ ነው፣ ለጊዝው አልፀዳም” አለ ኒልስ።

በርቲል ዙሪያውን ተመለከተ። አንድ መስኮት አለ፣ አጠገቡ አንድ ሰማያዊ የሸክላ ምድጃ ይታያል። በቃ… ሌላ ነገር የለም።

“አዎ! ይህን ቤት ከዚህ የተሻለ ማድረግ ይቻላል” አለ በርቲል በመስማማት። “ለመሆኑ ማታ ማታ የት ትተኛለህ?”

“ወለል ላይ ነዋ።”

““ወለል ላ! አይበርድህም?”

“መብረድ ብቻ! በጣም እንጂ። በብርድ እንዳልሞት በየሰዓቱ እየተነሳሁ ዱብዱብ እላለሁ።”


በርቲል ለኒልስ በጣም አዘነለት። እሱ ሌላ ቢቀር ማታ ማታ እንደ ኒልስ በብርድ አይሰቃይም። ወዲያውኑ አንድ ሃሳብ መጣለት።

“ምን ዓይነቱ ቂል ነኝ ባክህ፣ እንጨት ማምጣት እኮ እችላለሁ።”

ኒልስ የበርቲልን ክንድ ያዝ አደረገና “እውነት ትችላለህ!” አለ በጉግት።

“በደንብ” አለ በርቲል። “ችግሩ” አለ ትንሽ ሃዘን በሰበረው ቃና “ክብሪት መለኮስ የለብኝም።”

“ለሱ ግድ የለህም፣ አንተ ብቻ እንጨቱን አምጣ እኔ አቀጣጥለዋለሁ።“

በርቲል ደረጃውን በሩጫ ወጣና ሚስማሩን በጣቱ ነካ፣ ግን ያን የሚባለውን የይለፍ ቃል ረስቶ ኖሯል።

“ምን ነበር የምለው” ሲል ወደ ታች ወደ ኒልስ ጮኽ።

“ሺለቪፐን ነዋ” አለው ኒልስ።

“ሺለቪፐን ነዋ” አለ በርቲል ሚስማሩን ነካ አድርጎ፣ ግን ምንም ለውጥ የለም። ትልቅ መሆን ነበረበት ግን አልሆነም። እና ደነገጠ።

“ስማ ሺለቪፐን ብቻ በል” ኒልስ ከታች ወደ ላይ ጮኸ።

“ሺለቪፐን ብቻ” አለ በርቲል። አሁንም ምንም ለውጥ የለም። በርቲል ሚጢጢ ሆኖ የሚቀር መሰሎት ፈራ።

“አረ ባክህ!” ኒልስ ጮኽ፤ “ከሺለቪፐን በቀር ሌላ ነገር አትበል። ሰማህ!”

በርቲል ስህተቱ ገብቶት “ሺለቪፐን” ሲል ወዲያው ትልቅ ሆነ። ሲተልቅ አልጋው ስር ስለነበር አልጋው አናቱን አለው። ራሱን እያሸ በፍጥነት ከአልጋው ሥር ወጥቶ ወደ ኩችናው አመራ። ምድጃው አጠገብ ብዙ የተቃጠሉ የክብሪት እንጨቶች ነበሩ። እንጨቶቹን በትንንሹ ከሰባበረ በኋላ ወሰዶ አይጥ ቀዳዳው አጠገብ ከመራቸው። ከዚያ ‘ሺለቪፐን’ በማለት ራሱን አሳነሰና ኒልስን ጠርቶ “ናና አግዘኝ” አለው።

አሁን ሚጢጢ ከሆነ በኋላ እንጨቶቹን በሙሉ በአንዴ መሸከም አልቻለም። ኒልስ በደስታ እየዘለለ መጣና እንጨቱን ከላይ አውርደው ወደ ቤት ውስጥ፣ ከዚያም ወደ ሸክላው ምድጃ አጋጋዙ።

"አሪፍ እንጨት” አለ ኒልስ፣ “በውነት፥ እንጨት ማለት ይሄ ነው።”


ኒልስ ምድጃውን በእንጨት ከሞላ በኋላ የተረፈውን ምድጃው አጠገብ ግድግዳው ሥር አስቀመጠ።

“አሁን ታያለህ” አለና ምድጃው ፊት ለፊት ተንበርክኮ ደጋግሞ እፍ አለበት። አቤት! እንጨቱ ወዲያው መቀጣጠልና መንደድ ጀመረ።

“ወይ ብልሃት” አለ በርቲል እሳት እየሞቄ “ብዙ ክብሪት ያድናል ይሄ።”

“እንዴታ!” አለ ኒልስ “አቤት ደስ ሲል ... ግሩም እሳት! ክረምቱ ከገባ ጀምሮ እንዲህ ሞቆኝ አያውቅም።”

ከሚነደው እሳት ፊት ለፊት፤ ወለል ላይ ቁጭ ብለው በብርድ የተኮማተሩ ትንንሽ እጆቻቸውን ወደ ሚንበለበለው እሳት ዘርግተው ሞቁ።

“ብዙ እንጨት ቀርቶናል... አይደል?” አለ ኒልስ እርክት ባለ መንፈስ።

“አዎ! ሲያልቅ ደግሞ የፈለግነውን ያህል ማምጣት እችላለሁ።” አለ በርቲል እሱም ደስ ብሎት።

“ዛሬ በቃ፥ ሳይበርደኝ አድራለሁ።” አለ ኒልስ።

ከትንሽ ጊዜ በኋላ በርቲል “ለመሆኑ ምንድን ነው የምትበላው” ብሎ ሲጠየቀው፣ የኒልስ ፊት ቀላ።

“አ የተለያየ ዓይነት... ትንሽ ትንሽ” አለ በግማሽ ልብ። ከዚያ ትንሽ አስቦ “ባክህ ያገኘሁትን ነው የምበላው፣ አልመርጥም” አለ።

“ሌሜሆኑ ዛሬ ምን በልተህ ዋልክ?”

“ዛሬ?” አለ ኒልስ ራሱን እያከከ፣ “ዛሬ ምንም ነገር አልቀመስኩም።”

"ትላትስ?"

"ባክህ... እዚህ ከመጣሁ እህል አልቀመስኩም።"

“እንዴት! ታዲያ በጣም ተርበሃል ማለት ነዋ!” አለ በርቲል ድምፁን ከፍ አድርጎ።

“አዎ” አለ ኒልስ ፈራ ተባ እያለ “በጣም ርቦኛል”

“ታዲያ ለምን ቅድም አልተናገርክም ቂል! አሁን ሄጄ የሚበላ አመጣለሁ።”

ኒልስ፣ በደስታ ሊጮህ ምን አልቀረውም።

“ካደረከው… ዕውነት እምበላው ነገር ካመጣህልኝ በህይወት እስካለሁ ድረስ አልረሳህም።”


ኒልስ ይህን ሲል በርቲል ደረጃውን አገባድዶ ላይ ደርሶ ነበር። መውጫውን ከሾልኮ ከአልጋው ስር ወጥቶ ሺለቪፐን በማለት ራሱን አተለቀና በፍጥነት ማዕድ ቤት ውስጥ ካለው ምግብ ማስቀመጫ ሳጥን ደረሰ። ከዚያ ትንሽ ቅቤ ቆንጥሮ ትንሽ የዳቦ ቁራሽ ላይ ቀባና ያዘ። ትንሽ ደረቅ ቅቤ፣ አንድ ድቡልቡል ስጋና ሁለት የዘቢብ ፍሬዎችም ጨመረ። ሁሉንም ይዞ የአይጥ ጉድጓድ መግቢው አጠገብ ከደረደረ በኋላ ራሱን አሳነሰና ኒልሰን ጠራው።

“ናና ምግቡን አጋግዘኝ” በርቲለ ጮኸ። ግን በርቲል መጮኽ አያስፈልገውም ነበር፡ አጅሬ እዛው ቀሞ ይጠብቀው ነበር።

የኒልስ ዓይኖች ምግብ ሲያዩ በጉግት እንደ ክዋክብት አብለጨለጩ። ወዲያው የመጣውን ምግብ ተሸክመው ወረዱ።

በርቲልም ራብ ተስምቶት ሰለ ነበር፡ “በል በሥጋው እንጀምር” አለ።


ድቡልቡሉ ሥጋ የኒልስን ጭንቅላት ያህላል፣ እሱን ለሁለት ይዘው ማንኛቸው መሃል ቀድሞ እንደሚደርስ ተወራርደው ቶሎ ቶሎ ከየራሳቸው በኩል ይገምጡ ጀመር። ኒልስ መጀመሪያ ደረሰ። ከዚያ ቅቤ የጠጣውን ዳቦ አነሱ፣ ያ ትንሽ ቁራሽ ዳቦ አንድ አገር እክሎባቸዋል። እሱን እንዳጋመሱ ኒልስ ደረቁን ቅቤ ማስቀመጥ ፈለገ።


“ታያለህ! ለአይጧ የቤት ኪራይ የደረቅ ቅቤ ቁራሽ እከፍላታለሁ።” አለ ኒልስ “አለዚያ ታስወጣኛለች።”

“አይዞህ ለእሷ የሚሆን አናጣም፣ አሁን ዝም ብለን እንብላው።”


ደረቁንም ቅቤ ከበሉት በኋላ የየራሳቸውን አንዳንድ ዘቢብ ያዙ። ኒልስ ግን ግማሹን ዘቢብ ከበላ በኋላ “ነገ ከእንቅልፌ ስነሳ እበላዋለሁ” ብሎ የተረፈውን አስቀመጠ። “እንዲሞቀኝ ዛሬ እምድጃው አጠገብ ነው የምተኛው።”

ያኔ በርቲል ቀና አለና “አንተ፣ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፣ አንድ ግሩም ነገር” ብሎ ወዲያው ተነሳና ከቤት ወጣ።

ኒልስ ጠበቀ፣ በርቲል ግን ቶሎ አልተመለሰም። ቆይቶ፣ “ናና ይሄን አልጋ አግዘኝ” ብሎ ሲጮህ ኒልስ ሰማው።

ኒልስ ወደ ላይ ሲወጣ በርቲል አንድ ቆንጆ ነጭ አልጋ ይዞ አገኘው። የእህቱ ማርታ አሻንጉሊት ማስቀመጫ ሳጥን ውስጥ የነበረ አልጋ ነው። ዱሮ ትንሿ አሻንጉሊት የምትተኛበት አልጋ ነበር። አሁን የምር ፈላጊ አለው።

“የምትተኛበት ጥጥ ይዤልህ መጥቻለሁ… እናቴ ለኔ ቢጃማ ልታደርገው የነበረውን ጨርቅም አለ… እሱን እንደ ብርድ ልብስ ከላይ ትደርበዋለህ።“

“ኦ!” አለ ኒልስ፣ ሌላ ነገር መናገር አልቻለም።

“የአሻንጉሊቷን ሸሚዝም አምጥቼልሃለው። እና የቢጃማ ብታደርገው ቅር ይልሃል?”

“አይለኝም… ለምን ቅር ይለኛል።”

“ያው እንደምታውቀው የሴቶች እቃ ስለሆነ ምናልባት ደስ አይልህ ይሆናል ብዬ ነው።”

“ዋናው መሞቁ ነው” አለ ኒልስ፣ የአሻንጉሊት ልብሱን እየዳሰሰ “አልጋ ላይ ተኝቼ አላውቅም፣ አሁኑኑ ሄጄ መጋደም ፈለኩኝ።”

“ጥሩ፣ ተኛ። ወላጆቼ መምጫቸው ስለደረሰ እኔም ልሂድ።”

ኒልስ ልበሱን አወለቀ፣ የአሻንጉሊቷን ሸሚዝ አጠለቀና አልጋው ላይ ዘሎ ወጣ። ከዚያ ጥጡን እንደ ፍራሽ አድርጎ ላዩ ላይ ተኛና ብርድ ልብሱን ደረበ።

“ኦ! ተመሰገን! ጠገብኩ… ሞቀኝ… አሁን እንቅልፌ መጥቷል። በል ደህና እደር” አለው በርቲልን።

“ደህና እደር፣ ነገ እመጣለሁ።” አለ በርቲል።

ኒልስ ግን ወዲያው እንቅልፍ ወስዶት አልሰማውም።


በማግስቱ በርቲል፣ እናትና አባቱ እስኪሄዱለት መጠበቅ አልቻልም፣ ወደ ሥራ ሊሄዱ እግራቸው ወጣ ሲል ዘሎ አልጋው ስር ገባና ወደ ኒልስ ሮጠ። ኒልስ ተነስቶ ምድጃውን አቀጣጥሎ ነበር።

“የእንጨት ችግር የለም... አይደል?” ሲል በርቲልን ጠየቀው።

“በጭራሽ! እንዳሻ ማንደድ ትችላለህ… አታስብ።” ብሎ በርቲል ቤቱን አንዴ ቃኘው። “ታውቃለህ ይሄን ቤት ማስመር እንችላለን እኮ!”

“አዎ ይቻላል… ወለሉን ታያለህ ተወልውሎ የሚያውቅ አይመስልም።”

ኒልስ ተናግሮ ሳይጨርስ፣ በርቲል በሩጫ ደረጃውን ወጣና ላይኛው ቤት ገባ። አንድ ወለል መፈግፈጊያ ብሩሽና አንድ መወልወያ ጨርቅ ነበር የሚያስፈልገው። ማድቤት ውስጥ ከእቃ ማጠቢያው አጠገብ አንድ አሮጌ የጥርስ ብሩሽ አገኘ። እሱን አነሳና እጀታውን ሰበረ። ከዚያ የእቃ ሳጥኑን ከፈተ። እዚያ ውስጥ ደግሞ እናቱ ቅባት የምታቀርብበት ትንሽ ስኒ አለ፣ እሱን ወስዶ ሙቅ ውሃ ሞላበትና አንድ ጠብታ ፈሳሽ ሳሙና ጨመረበት። የቤት ማፀደጃ እቃዎች ከሚቀመጡበት ጓዳ ውስጥ ደግሞ ከመወልወያው ጫፍ ላይ ትንሽ ጨርቅ ቆረጠ።


ሁሉንም ተሸከሞ እንደ ልማዱ ከአይጥ ጉድጓድ ቀዳዳ አጠገብ ደረደረ። ኒልሰም ወዲያው መጥቶ እቃውን ተጋግዘው ወደ ታች አወረዱ።

“ትልቅ ብሩሽ ነው ያመጣኽው” አለ ኒልስ

“አዎ ጥሩ አድርጎ ይፍቅልናል።”


ሁለቱም ሥራ ጀመሩ፣ በርቲል በብሩሽ ሲፈገፍ ኒልስ ጨርቅ እያረጠበ መወልወል ያዘ። ሰኒው ውስጥ የነበረው ውሃ ጠቆረ ግን ወለሉ ጸድቶ እንደ መስታወት አብለጨለጨ።

“አሁን ደረጃው ላይ አርፈህ ቁጭ በል” አለው በርቲል አፅድተው እንደጨረሱ “አንድ አስደናቂ ነገር ታያለህ… ዓይንህን ብቻ ጨፍን… እንዳታይ።” ብሎ በርቲል ላይ ቤት ሄደ።

ኒልስ ዓይኖቹን በእጁ ጨፍኖ በርቲል ላይ ቤትና ታች እየተመላለሰ ሲንጎዳጎድ የማየትጉጉቱ በጣም ጨመረ። በርቲል ብዙ ሲንጎዳጎድ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ “አሁን ማየት ትችላለህ” አለው

ኒልስ እጁን አነሳ። ቤቱ ሌላ ሆኗል፣ ጠረጴዛና ወንበር አንድ ቁምሳጥን፣ ሁለት ትንንሽ አግዳሚ ወንበሮች፣ ሁለት ክምር ማገዶ ገብቷል።

“ሚስት ነች የቀረችን፣ የታለች” ኒልስ በደስታ ጮኸ። “እሷንም በአሰማት ታመጣልኛለህ”

በርቲል መቼም ያን ማድረግ አይችልም። ይሄን ሁሉ ዕቃ አንኳን ያገኘው ከእህቱ ከማርታ አሻንጉሊት ሳጥን ውስጥ ነበር። ምንጣፋ አምጥቷል፣ ባለ መስመር ምንጣፍ- እሱም ማርታ የፈተለችው ነበር።


መጀመሪያ ምንጣፋን ወለል ላይ ዘርጉ፣ ወለሉን በሙሉ ሊሸፍን ምንም አልቀረውም።

“እንዴት ያምራል።” አለ ኒልስ ምንጣፉን አይቶ። “ጠረፔዛውና ወንበሮቹ መሃል ላይ፣ ቁምሳጥኑ በጥግ፣ ሁለቱ ዱካዎች ደግሞ ምድጃው አጠገብ ሲቀመጡ ይበልጥ ያምራል።” አለ ኒልስ ትንፋሽ እያጠረው።


በርቲልም የቤቱን ማማር ተገንዝቧል፣ ከላይኛው ከራሱ ቤት ባላነሰ ያማረ መሰሎ ታየው።

“አሁን ራስን ደሞ ትንሽ ማሳመር ያስፈልጋል” አለ ኒልስ “እንዲህ እንደኔ መቆሸሽ አይገባም።”

“አዎ ገላችንን እንታጠባ።”

ወዲያው በስኒው ሙቅ ውሃ ተሞልቶ መጣ። አንድ አሮጌ መሃረብም ቆንጆ የገላ ማድረቂያ አንሶላ ወጣው። ወሃ በደረጃው ይዘው ሲወርዱ ተንጠባጥቦ ነበር ግን የቀረው ለመታጠቢያ በቂ ነበር። ከዚህ በኋላ ልብሳቸውን አወላልቀው ባኞው ውስጥ ገቡ። አቤት! እንዴት ደስ ይላል።

“ጀርባዬን እሽልኝ” አለ ኒልስ።

ተራ በተራ ጀርባቸውን ተሻሹ። ውሃም ወለል አምቦራጭቁ፣ ግን ምንም ነገር አልተበላሸም፣ ምንጣፋን ጠቅልለው ጥግ አስይዘው ነበር። ሳንቃው ደሞ ቀስ ብሎ መድረቁ አይቀርም።

በመጨረሻ አንሶላውን ላያቸው ላይ ጠቅልለው ወጡ። ከዚያ ዱካዎቹ ላይ ቁጭ ብለው የባጥ የቆጡን እያወሩ፣ እሳት ሞቁ። በመሃል በርቲል አንዴ ሮጦ ስኳርና የድንች ቁራሽ ይዞ መጣና ድንቹን እሳት ላይ ጠበሱ። ግን ብዙም ሳይቆይ በርቲል-- ወላጆቹ ወደ ቤት መምጫቸው ጊዜ መድረሱን አስታወሰና ከድንቹ ምንም ሳይበላ ልብሱን ለመልበስ ተጣደፈ። ኒልስም የራሱን ለበሰ።


“አብረን እላይ ብንሄድ መቼም ድንቅ ነበር” አለ በርቲል “ሸሚዜ ኪስ ውስጥ ብትገባ ማን ያይሃል።”

ኒልስ የሰማውን ለመተግበር በጣም ጓጓ። “እንዴታ አርፌ ቁጭ ካልኩ ማን ያየኛል።”

በዚህ ተስማምተው ወደ ላይኛው ቤት ተያይዘው ሄዱ። እላይ ቤት እንደደረሱ በርቲል ኒልስን አንስቶ ሸሚዙ ኪስ ውስጥ ወሸቀው።

ከትንሽ ጊዜ በኋላ እናትና አባት መጡ። የራት ሰዓት ደረሰ። ሁሉም የምግብ ጠረጴዛውን ከብበው ተቀመጡ።

“ምነው ልጄ- ምን ነካህ... ፀጉርህ ረጥቧል።” አለች እናትየው፤ መብላት ሲጀምሩ።

“አዎ - ገላዬን ታጥቤአለሁ” አለ በርቲል።

“ገላዬን ታጥቤአለሁ? ሆ! የት ነው ደሞ የታጠብከው?”

“እዚህ ውስጥ” አለ በርቲል እየሳቀ፣ አሁን ቅቤ ይዞ ጠረፔዛው ላይ የተቀመጠውን ስኒ እያመለከተ።

እናትና አባቱ እየቀለደ ነው ብለው አስበዋል። “በርቲል እንዲህ ደስ ብሎት ማየት… ደስ ይላል” አለ አባትየው።

“በጣም እንጂ” አለች እናቱ “ቀን ቀን ብቻው ሲውል በጣም ያሳዝነኛል።”

ሸሚዙ ውስጥ አንድ ነገር ሲንቀሳቀስ ተሰማው፣ በርቲል። ሞቅ ያለ ነገር፣ በጣም የሚሞቅ ነገር።

“እማዬ፣ አታስቢ ብቻዬን ስሆን'ኮ አይካፋኝም፥ እንዲያውም ደሰ ይለኛል”። አላትና ጣቱን ሸሚዙ ውስጥ ከትቶ ኒልስ ካርልሶን- ሚጢጢውን ዳበሰው ….

Welcome

Recent Blog Entries

Newest Members

Donate! for the film making

  • No current campaigns

Recent Forum Posts